የግማሽ ዳሌ መገጣጠሚያ ቅየራ / ሄሚአርትሮፕላስቲ

ይህ ራጅ የ80 አመት አዛውንት የዳሌ አንገት ላይ የተከሰተን ስብራት እና ዶ/ር ሳሚ የግማሽ ዳሌ መገጣጠሚያ ከቀየረላቸው በሗላ ያሳያል።

የዳሌ መገጣጠሚያ ኳስ የሚመስል ራስ እና ማቀፊያ ያለዉ (ball and socket joint) መገጣጠሚያ ነዉ። የዳሌ ራስ መሰኪያዉ የዳሌ ማቀፊያ (Acetabulum) በመባል የሚታወቅ ሲሆን ይሄዉም የላይኛዉን የታፋ አጥንት አናት (femoral head) እንደማቀፊያ ይይዘዋል።

ለታፋ አጥንት ራስ የሚደርሰዉ የደም ዝውውር ሳሳ ባለዉና የላይኛዉን እና የታችኛዉን የእጥንቱን ከፍል በሚያገናኝ ክፍል ያልፋል። ይህም የአጥንት ክፍል የስብራት አደጋ በሚደርስበት ጊዜ የደም ስሩ ላይ አደጋ በማድረስ የደም ዝዉዉሩ ሊቋረጥ ይችላል። ስብራቱ ቀዶ ህክምና ቢደረግም የደም ዝውውሩ የመመለሱ እድል ዝቅተኛ ነዉ። የደም ዝውውር ያጣዉም የአጥንቱ አናት ሊበሰብስ ይችላል። ይሄንንም በደም ዝውውር እጥረት የሚከሰት የዳሌ ራስ መበስበስ (AVN- Avascular Necrosis) ተብሎ ይጠራል።

እድሜያቸው በገፋ እና አጥንት መሳሳት ባለባቸው ሰዎች የዳሌ አንገት ስብራት በሚያጋጥማቸው ጊዜ የዳሌ ራስ መበስበስ ወይም ስብራቱ ያለመዳን እድል ይኖረዎል። ስለሆነም ቦታውን የለቀቀ የዳሌ አንገት ስብራት ከ50ዓመት በላይ የሆናቸው ሰዎች ላይ በብራት የማያያዝ ቀዶ ህክምናን አንመክርም። ይልቁንም የዳሌ ራስ ይወገድና በሰዉ ሰራሽ አካል ይተካል። ይሄንንም ተመራጭ የሚያደርገዉ ምክንያት ለስብራቱ በብረት ቢጠገን ባለመዳን ወይም በመበስበስ ምክንያት እንደገና ቀዶ ህክምና የመደረግ እዱሉ ከፍተኛ በመሆኑ ነዉ።

እንደ ኳስ ቅርጽ ያለዉ ሰዉ ሰራሽ ክፍል ከተፈጥሯዊው የዳሌ ማቀፊያ ጋር ይገጥማል። ይሄኛዉም አሰራር ሁለቱንም አናቱንም ሆነ ማቀፊያዉን ከመቀየር ይልቅ ቀለል ያለ እና የቀዶ ህክምናውም ጫና የቀነሰ ይሆናል። ስለሆነም እድሜያቸው በጣም በገፋ እና ተጓዳኝ የጤና ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ ግማሽ የዳሌ መገጣጠሚያ ቅየራ ከሙሉ መገጣጠሚያ ይልቅ ተመራጭ ነው። ታካሚዎቹንም ከቀዶ ህክምና በኋላ በአጭር ጊዜ እንቅስቃሴ አንዲጀምሩ ያስችላል።

እድሜ ገፋ ካለ በኋላ የሚከሰት የዳሌ አጥንት ስብራት ጉዳቱ መሰበር ብቻ ሳይሆን ህይወትን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ተጓዳኝ ጠንቆችን ሊያስከስት ይችላል። በፍጥነት (ከ 3ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ) ቀዶ ህክምና ማድረግ እና እንቅስቃሴን በፍጥነት ማስቀጠል አልጋ ቁራኛ በመሆን የሚመጡ ችግሮችን ያስቀራል።

ዶ/ር ሳሜኤልም የግማሽ ዳሌ ቅየራ ቀዶ ህክምናን ጉዳቱ መጠነኛ በሆነ አሰራር ማለትም ጡንቻ ሳይቆረጥ፥ ከፊት ለፊት በሚደረግ ቀዶ ህክምና በሀገረ አሜሪካ የሚሰሩ ሰዉ ሰራሽ አካላትን በመጠቀም ያከናዉናል። አብዛኛቹ ታካሚዎቻችን እንደየ አካላዊ ጤንነታቸዉ አኳያ በአጭር ጊዜ ማለትም ከስብራት በሀላ ከ 24 እስከ 48 ሰዓታት ዉስጥ ቀዶ ህክምናቸዉ ሊካሄድ ይችላል። አብዛኞቹም ታካሚዎቸችን ከሁለት ቀናት ቆይታ በኋላ ወደ ቤታቸዉ ይመለሳሉ።

የግማሽ ዳሌ ቅየራ ህክምና እንዲደረግልዎ በሃኪም ከተመከሩ ከ ዶ/ር ሳሙኤል ጋር ስለ አስፈላጊነቱ እና የተለያዩ አማራጮች ህክምናዎች ለማግኘት በማንኛውም ሰዓት ለድንገተኛ ስብራት ህክምና ወደ ሳማሪታን መምጣት ይችላሉ። እያንዳንዱ ቀዶ ህክምና የራሱ የሆነ የሚያስከትለዉ ተጓዳኝ ችግር ሊኖር ስለሚችል የቀዶ ህክምናዉ አስፈላጊነት ላይ በስርዓት ከዶ/ር ሳሙኤል ጋር መመካከሩ ይበጃል።

ስለ ዳሌ አንገት ስብራት፣ መከላከያ እና ህክምና የበለጠ ለመረዳት ከስር በዶ/ር ሳሜኤል የተዘጋጀዉን የቪድዮ ገለጻ ይመልከቱ።

የቀዶ ህክምና አማራጮቹን የበለጠ ለማወቅ ከስር ዶ/ር ሳሙኤል በ ኢቲቪ ጤናዎች በቤትዎ ፕሮግራም ያደረጉትን ቃለመጠይቅ ይመልከቱ።

በ ሃምሌ 2013 ዓ.ም በዶ.ር ሳሙኤል ኃይሉ የተዘጋጀ እና የቀረበ

*ማስታወሻ:* በዚህ ጽሁፍ የተዘጋጀዉ መረጃ ለማስተማሪያነት የሚዉል ነዉ። ይሄም ጽሁፍ ሀኪም ማማከርን ሊተካ አይገባም። በዚህ ጽሁፍ ላይ ባገኙት መረጃ ምክንያት በኃኪምዎ የታዘዙትን ምክር ወደ ጎን መተዉ አይመከርም።

Send this to a friend