ውልቃቶች

ምንድነዉ?
ውልቃት ማለት ሁለት መገጣጠሚያ ላይ የሚገኙ በሁለቱም በኩል ያሉ የአጥንት ክፍሎች መለያየት ነዉ። በአብዛኛዉ ዉልቃት የሚከሰትበት መገጣጠሚያ የትከሻ መገጣጠሚያ ሲሆን በሌሎች መገጣጠሚያዎችም፤ ማለትም በ ጣቶች፣ ክንድ፣ ጉልበት እና ዳሌ መገጣጠሚያዎች ላይም ሊከሰት ይችላል።
መንስኤ
አብዛኛዉን ጊዜ የዉልቃት መንስኤዎች ከፍተኛ ሃይል ያላቸዉ አደጋዎች ሲሆኑ በ ስፖርት ወይም በመዉደቅ ጊዜ ሊከሰቱ ይችላሉ። ነገር ግነ አብዛኛዉን ጊዜ የሚከሰተዉ የትከሻ መዉለቅ ነዉ።
ምልክቶች
ለመጀመሪያ ጊዜ መገጣጠሚያ መዉለቅ ባጋጠመበት ቦታ ላይ ከፍተኛ የሆነ የህመም ስሜት የሚሰማ እና ዉልቃቱ የደረሰበት መገጣጠሚያ ላይ አጥንቶች ቦታ መሳት ይታይበታል። ከዚያም በተጨማሪ ለማንቀሳቀስ እጅግ ከባድ ሊሆን ይችላል። በተደጋጋሚ ዉልቃት የደረሰበት መገጣጠሚያ ከጊዜ ወደ ጊዜ የህመም መሰማቱ መጠን እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል። በዚህም ጊዜ የችግሩ ምልክት የሚሆነዉ የአጥንቶች ቦታ መሳት እና ማንቀሳቀስ መሳን ይሆናል።
ምርመራ
አብዛኛዉን ጊዜ መገጣጠሚያ ላይ ያሉ አጥንቶች ቦታቸዉን መሳታቸዉን መጠቆም ከባድ አይደለም፣ ነገር ግን የሚበቃ መረጃ ከወሰድን እና አካላዊ ምርመራ ካደረገን በኋላ የራጅ ምርመራ ልናደርግ እንችላልን።
የራጅ ምርመራ ብዙ ጊዜ የአንጥንት ቦታ መሳትን ያሳያል፣ አልፎ አልፎ በተወሱ ዉልቃቶች በተላለያዩ አቅጣጫዎች ራጅ ምርመራ ሊያስፈልገን ይችላል።
የሲቲ ስካን የዉልቃቱን ሁኔታ ለመረዳት እና ከዉልቃቱ ጋር ተያይዞ ያሉ ሌሎች ጉዳቶች ካሉ እና በራጅ ምርመራ ያልተገኙ ከሆነ እነዚህን ለመለየት ያገለግላል። .
ኤም አር አይ ምርመራ ደግሞ በዉልቃቱ ዙሪያ ያሉ ጡንቻዎች ጉዳትን ለመጠቆም ይረዳል። ከዉልቃት ሳምንታት በኋላ በሚመጡ ታካሚዎች ላይም ኤም አር አይ ላዝላቸዉ እችላለሁ። ይሄም ደግሞ የላይኛዉ ታፋ አጥንት ራስ ጤንነትን እና የቀዶ ህክምናዉን አይነትም ለመወሰን ይረዳኛል። ከላይ በምስሉ ላይ ያያችሁት ራጅ ከ 6 ሳምንታት የቆየ የዴ ዉልቃት በኋላ ውደ ህክምና የመጣ ወጣት ነዉ። በ ኤም አር አይ ምርመራዉ ላይ ግን የ ላይኛዉ ታፋ አጥንት ራስ ደህና እንደሆነ ስላሳየን የዳሌ መገጣጠሚያዉን ወደ ቦታዉ ያለ ዳሌ ቅየራ ወደ ተፈጥሮዉ ቦታ ለመመለስ ችለናል።
ህክምና
የመገጣጠሚያ ዉልቃቶች በአፋጣኝ ህክምና ከሚያስፈልጋቸዉ የአጥንት ህክምና ችግሮች መካከል ይመደባለ። የመገጣጠሚያ ላይ የሚገኙ ክፍሎች የራሳቸዉ የሆነ ደም ስር ስለ ሌላቸዉ ከአቅራቢያቸዉ የሚገኙ ክፍሎች ስለሆነ ምግብ እና ኦክሲጅን የመሚያገኙት በመገጣጠሚያ ዉልቀት ጊዜ በዚህ ስርዓጥ ላይ ችግር ሊፈጠር ይችላል። ይሄም ደግሞ በህይወት የመቆየታቸዉን ጉዳይ አሳሳቢ ስለሚያደርገዉ ቀዶ ህክምናዉ እና የዉልቃት ማስተካከያዉ በተቻለ ፍጥነት መካሄድን አስፈላጊ ያደርገዋል።
አፋጣኝ የሆነ ያለ ቀዶ ህክምና የሚደረግ እርዳታ በቂ የጡንቻ ማደንዘዣ በመስጠት እና ጡንቻዎችን ለቀቅ በማድረግ የመገጣጠሚያዉን አጥንቶች ወደ ቦታቸዉ መመለስ ይቻላል።
የቀዶ ህክምና እርዳታ የሚያስፈልገባቸዉ ሁኔታዎች፡-
- ወደቦታቸዉ መመለስ የሚያዳግቱ የሚገጣጠሚያ አጥንቶች
- ቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸዉ ስብራቶች አብረዉ የተከሰተባቸዉ የመገጣጠሚያ ዉልቃቶች
- ቆየት ብሎ ወደ ህክምና የሚመጡ ታካሚዎች ላይ የመገጣጠሚያዉ አካላት ላይ ሚከሰተዉ ጠባሳ አጥንቶቹን ወደ ቦታቸዉ ለመመለስ የሚያዳግት ከሆነ፣
- በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ዉልቃቶችን ለማከም
- ከዉልቃቱ የተነሳ የመሚከሰቱትን ቁርጥማትን እና ደም ከማጣጥ የተነሳ የሚከሰተዉን የአጥንት መበስበስን ለማከም
የዶ.ር ሳሙኤልም ትኩረት አቅጣጫ በ ዳሌ እና ክንድ ዉልቃት ህክምናዎች ነዉ። ከስራ ባልደረቦቹም ጋር በመሆን ቆየት ብለዉ ለሚመጡ የክንድ መገጣጠሚያ ዉልቃት ችግሮች መፍትሄ የሚሆን ቴክኒክ የሚያትት ጥናት አሳትመዋል። ይሄም ስራቸዉ በአሜሪካ የ አጥንት አደጋ ህክምና ማህበር ምርጥ ጥናት በመባል በጥቅምት 2008 ዓ.ም ተሸላሚ አድርጓቸዋል።
ቆየት ብለዉ በሚመጡ የዳሌ ዉልቃቶችም ላይ እየሰሩባቸዉ ያለዉም ህክምና ቴክኒክ ጥናትም በተወሰኑ ታካሚዎች ላይ አመርቂ ዉጤት እያሳየ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪም ዶ.ር ሳሙኤል የአጥንት መበስበስ ላስከተሉ የዳሌ መገጣጠሚያ ዉልቃቶች፣ ቁርጥማት እና አንዳንድ የተወሰሰቡ ስብራቶችን ላስከተሉ ትኩስ የዳሌ ዉልቃቶችም የዳሌ ቅየራ ቀዶ ህክምናን እያደረጉ ይገኛሉ።
በ ሃምሌ 2013 ዓ.ም በዶ.ር ሳሙኤል ኃይሉ የተዘጋጀ እና የቀረበ
*ማስታወሻ:* በዚህ ጽሁፍ የተዘጋጀዉ መረጃ ለማስተማሪያነት የሚዉል ነዉ። ይሄም ጽሁፍ ሀኪም ማማከርን ሊተካ አይገባም። በዚህ ጽሁፍ ላይ ባገኙት መረጃ ምክንያት በኃኪምዎ የታዘዙትን ምክር ወደ ጎን መተዉ አይመከርም።
