የሰብአዊ ምሁር ተሸላሚ

ዶ/ር ሳሙኤል ኃይሉ ከጥቅምት 11-13፥ 2014 በአሜሪካ ቴክሳስ በተካሄደው 37ኛው የአጥንት አደጋዎች ህክምና ሰብ-ስፔሻሊስቶች ማህበር አመታዊ ሳይንሳዊ ጉባኤ ላይ “የሰብአዊ ምሁር ሽልማት” ተቀበለ።

ይህ ጉባኤ የአጥንት አደጋወች ሰብ-ስፔሻሊስቶች ማህበር ሲሆን በአደጋ ምክንያት የሚከሰቱ ጉዳቶችን በላቀ ሁኔታ ለማከም ያስችል ዘንድ በጥናቶች በተደገፈ መልኩ የሚሰራ ማህበር ነው።

ዶ/ር ሳሙኤል እንደ አውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠር ከ2016 እስከ 2017 ባሉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ብቸኛው የዳሌ አጥንት ስብራት ሰብ-ስፔሻሊስት የነበሩበት ጊዜ ሲሆን፤ ተሸላሚ ያደረገቸው የምርምር ስራ በአጥንት ህክምና በውስብስብነቱ የሚታወቀው የዳሌ መገጣጠሚያ ማቀፊያ ስብራት ቀዶ ህክምና ነው። ይህ ቀዶ ህክምና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ቢያስፈልገውም፥ ያለ እነዚህ ግብዓቶች በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ያከናወኗቸውን ስራወች አመርቂ ውጤት የቃኘ ነው።

ይህን ሕክምና ውስብስብ የሚያደርገው የአጥንቱ አፈጣጠር እና በዙሪያው በሚገኙ የደም ስሮች እና ነርቮች አካላዊ አቀማመጥ የተነሳ ነው። ስብራቱም በቀዶ ሕክምና በሚሰራበት ጊዜ አላስፈላጊ ጉዳት እንዳያስከስት እና ወደ ሚፈለግበት ቦታ እንዲመለስ የቴክኖሎጂ ድጋፍን ይፈልጋል። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ውስጥ እነዚህን ቴክኖሎጅዎች በቀላሉ ማግኘት አይቻልም። ስለሆነም ዶ/ር ሳሙኤል እነዚህን የተወሳሰቡ ጉዳቶችን ያለ እነዚህ የቴክኖሎጅ ድጋፎች ለማስተካከል ተገዷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከ585 በላይ የዳሌ ገንዳ እና ማቀፊያ ስብራት ያለባቸውን ህሙማን በሁለት አመታት ውስጥ ያከመ ሲሆን። ከእነዚህ ጉዳቶች ውስጥ 202 የሚሆኑት የዳሌ ማቀፊያ ስብራት የነበራቸው ሲሆን። ከነዚሀም ውስጥ 108 ያህሉ በቀዶ ህክምና ጊዜ የሚያስፈልገው ራጅ በሌለበት ሁኔታ ቀዶ ጥገና አድርጎላቸዋል። ከቀዶ ጥገናውም በኋላ እነዚህን ታካሚዎች ከሁለት እስከ አራት ዓመታት ተከታትሏል።.

የቀዶ ህክምናውም የክትትል ውጤት ሁሉም ነገር በተሟላበት ሆኔታ ስብራቱ ከሚሰራባቸው ሀገራት የምርምር ወጤት ጋር ሲነጻጸር በተመሳሳይ ወይም በተሻለ ሆኔታ አመርቂ ውጤት አሳይቷል።

የህንንም ለማከናወን በተለያየ ደረጃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱለት መምህሮቹ፥ የሙያ አጋሮቹ፥ እና ድጋፍ ሰጭ ግለሰቦች እንዲሁም የእርዳት ድርጅቶች ላቅ ያለ ምስጋናን አስተላልፏል።

Leave a Comment

Send this to a friend