ብዙ ቦታ ላይ የሚከሰቱ ዉስብስብ ስብራቶች

3ኛ ፎቅ ላይ በመውደቁ ምክንያት አንድ ታካሚ ላይ 5 ቦታ (ማለትም ዳሌ ገንዳ ከ ኋላ እና ከፊት፣ ዳሌ ማቀፊያ፣ የአግር ቅልጥም፣ የተረከዝ መረገጫ አጥንት) ላይ የደረሱ ዉስብስብ ስብራቶችን የሚያሳይ ሲቲ ስካን እና በትንሽ ጠባሳ 5ቱም ቦታላይ የደረሱት ስብራቶች በዶ/ር ሳሙኤል በአንድ ቀዶ ህክምና ከተሰሩ በኋላ የሚያሳይ ራጅ።

ምንድነዉ?

ብዙ ቦታ ላይ የሚከሰቱ ዉስብስብ ስብራቶች ከፍተኛ የሆነ ሀይል ያለዉ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ብዙ አጥንቶች ላይ በ አንዴ የሚከሰት የስብራት ዓይነት ነዉ። ይሄም ጉዳት በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚከሰቱ ስብራቶችን እና የሌሎች የሰዉነት ክፍሎችንም ጉዳት ሊያካትት ይችላል። እነዚህም ጉዳቶች በአብዛኛዉን ጊዜ ህይወትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ እና የታካሚዉን ህይወት ለመታደግ የተለያዩ የህክምማ ባለሙያዎች የህብረት ስራ የሚፈልግ ሊሆን ይችላል።

መንስኤ

ከፍተኛ ፍጥነት ያለዉ መኪና አደጋ ወይም ከከፍታ ላይ መዉደቅ ዉስብስብ ስብራቶችን ሊያስከትል ይችላል።

ምልክቶች

እነዚህ ህይወትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ስብራቶች ምልክቶቻቸዉ እንደየስብራቱ ደረጃ እና ሰዉነት ክፍል ከሚሰሙ ህመሞች ህይወት እስከማለፍ ሊያደርሱ ይችላሉ። አጠቃላይ ጤንነታቸዉ ላይ ችግር የሌለባቸዉ የሚመስሉ ታካሚዎች እንኳን በድንገት ጤናቸዉ አደጋ ዉስጥ ሊገባ ስለሚችል በሆስፒታል ውስጥ ጥብቅ ክትትል አንዲደረግላቸዉ ያስፈልጋል።

ምርመራ

ሁሉም ከፍተኛ ሃይል ያላቸዉ አደጋዎች እንደ መጀመሪያ ምርመራ የራጅ ምርመራ ሊደረግላቸዉ ይገባል። የራጅ ምርመራዎችም፡- የደረት፣ የዳሌ ገንዳ፣ የአንገት ራጅ ምርመራ፣ ከአደጋዉ የሰዉነት ስፍራ በተጨማሪ የራጅ ምርመራ ሊደረግ ይገባል። የራጅ ምርመራም የአጥንት ጉዳቶችን ወይም ስብራቶችን ማሳየት ቢችልም በተቻለ መጠን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሊታይ ይገባል።
የሲቲ ስካን የዉልቃቱን ሁኔታ ለመረዳት እና ከዉልቃቱ ጋር ተያይዞ ያሉ ሌሎች ጉዳቶች ካሉ እና በራጅ ምርመራ ያልተገኙ ከሆነ እነዚህን ለመለየት ያገለግላል። የጉዳቱን ሁኔታንም ከተለያየ አቅጣጫ (3D) ለመቃኘት ይረዳል። እንደየ አስፈላጊነቱም የአልትራሳዉንድ እና ኤም አር አይ ምርመራም ሊታዘዝ ይችላል።

የተለያዩ የደም ምርመራዎችንም በማድረግ የፈሰሰዉን የደም መጠን ለመለካት እና የጉበት፣ ኩላሊትንም ጤንነት ለማወቅ ይረዳል። የሽንት ምርመራም በማድረግ የሽኝት ቧንቧ ላይ የደረሰ አደጋ ካለ ለማወቅ አስፈላጊ ይሆናል።

ህክምና

በመጀመሪያ ደረጃ ህይወትን የመታደግ ህክምና ቅድምያ የሚሰጠው ሲሆን፤ ለህይዎት አስጊ የሆነ ችግር ከተቀረፈ በኋላ በተቻለ መጠን የቀዶ ህክምና ጉዳቱ መጠነኛ በሆነ ቀዶ ህክምና በማድረግ የተጎዳዉን አካል በትንሽ ጠባሳ ማከም ተመራጭ ነው።

1. በአደጋው ጊዜ የህይወት የማትረፍ እርዳታዎች

ድንገተኛ አደጋዎች በተለያዩ የሰዉነት ክፍሎች ህይወትን አደጋ ዉስጥ ሊያስገቡ የሚችሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህም በአደጋ ጊዜ የሚደረጉ የህይወት ማትረፍ እርዳታዎች አላማቸዉ ይሄ እንዳይከሰት ማድረግ ነዉ።

 • አንገትን በትክክለኛዉ ቦታ በማድረግ እንቅስቃሴን ማስወገድ
 • የሚፈስን ደም ማስቆም
 • የፈሰሰዉን ደም መተካት
 • ስብራቶችን በመጀመሪያ ደረጃ አጥንቶችን አላስፈላጊ እንቅስቃሴ መግታት
 • ክፍት የሆኑ ቁስሎች በሚከሰቱበት ጊዜ የጸረ ባክቴሪያ መድሃኒቶችን መስጠት
 • እንቅስቃሴ ከመገታቱ የተነሳ ደም እንዳረጋ የደም ማቅጠኛዎችን እንደ አስፈላጊነቱ መስጠት ይገኙበታል።

በተገቢዉ ፍጥነት ወደ ህክምና እርዳታ ቦታዎች ላይ ታካሚዉን ማድረሱ እጅግ ቁልፍ ሲሆን፤ በተጨማሪም ክፍት ለሆኑ ቁስሎች ተገቢዉን ጸረ ባክቴሪያ መስጠት እና ደም ማቅጠኛ መድሃኒቶች እጅግ ጠቃሚ ናቸዉ።

ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ጉዳቶችን ከተቆጣጠርን በኋላ የተሰበሩ አጥንቶች ወደቦታቸዉ በተሻለ ሁኔታ እንዲመለሱ በማድረግ እንዲድኑ ማድረግ ላይ እናተኩራለን።

2. የስብራቶቹ ህክምና

ውስብስብ የሆኑ ስብራቶች ቀዶ ህክምና ከህክምናዉ በኋላ ሊከሰት የሚችለዉን ጉዳት ለመቀነስ የራሱ የሆነ ስርዓተ መንገዶች ይከተላል። እነዚህም መንገዶች ከሚከተሉት ሁለቱ አንዱ ሊሆን ይችላል።

ደረጃን በጠበቀ መልኩ የሚደረግ ህክምና

ዉስብስብ የሆነ ጉዳት የደረሰባቸዉ ታካሚዎች ሌላ ተጓዳኝ ጉዳት የደረሰባቸዉ እና ቀዶ ህክምና ልናደርግባቸዉ የማንችል ከሆነ፣ የህይወት አድን እርዳታ እያደረግንላቸዉ ጊዜያዊ የሆነ አጥንታቸዉን ወደ ቦታዉ መመለስ ህክምና ልንሰራላቸዉ እንችላለን። ይህም በሚከተሉት ሊከናወን ይችላል፡-

 • ያለ ቀዶ ህክምና፡ በተለያዩ መወጠሪያዎች ወይም ማሰሪያ ድጋፎች፤
 • በቀዶ ህክምና፡-
  • ከዉጭ የሚደረግ ድጋፍ /External fixation: በቆዳ አልፎ የሚወጡ ብረቶችን በመጠቀም እና ከሰዉነት ዉጪ ስብራቶቹን መደገፍ እንደ መጀመሪያ ደረጃ ድጋፍ ሊወሰድ ይችላል።
  • በቆዳ ስር የሚደረግ ድጋፍ /Percutaneous fracture stabilization: ስብራቶቹ ጉዳቱ መጠነኛ በሆነ ዘዴ ቀዶ ህክምና ሊደረግባቸዉ የሚችሉ አይነት ከሆኑ አላስፈላጊ ደም መፍሰስን እና የዉስጥ ሰዉነት አካላትን ጉዳት ሳያስከትል በዘላቂነት በዚህ መንገድ ህክምና ሊደረግላቸዉ ይችላል።
 • በመጀመሪያ ደረጃ አጥንቶቹ ድጋፍ ከተደረገላቸዉ በኋላ ታከሚዉ ቀዶ ህክምና ማድረግ የሚቻልበት የጤንነት ደረጃ ላይ ሲደርስ ቀጣይ ቀዶ ህክምና በማድረግ ዘላቂ ድጋፍ ይደረግለታል።

ባንዴ የሚደረግ አጠቃላይ ህክምና

አጠቃላይ ጤንነታቸዉ ደህና በሆኑ እና መጠነኛ ጉዳት ባላቸዉ ታካሚዎች ላይ ሁሉንም ስብራቶች ቀዶ ህክምና ወዲያዉ ሊደረግ ይችላል። ወዲያዉ የሚደረገዉ ዘላቂ ቀዶ ህክምና እንደሚከተሉት ሊደረግ ይችላል፡-

 • ጉዳቱ መጠነኛ በሆነ መልኩ:

በትንሽ ጠባሳ የሰውነት ቀዳዳዎችን በመብሳት ቆዳ ስር በሚቀበሩ ሰዉ ሰራሽ በሆኑ ቁሶች ስብራቱ ይደገፋል። የተለያዩ መጠነኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ዘዴዎችን በመጠቀም የተራራቁ ስባሪ አጥንቶችን በማጠጋጋት መደገፍ ይቻላል። ይሄም ዘዴ የደም መፍሰስን ከመቀነሱም በላይ ከከባድ ስብራት በኋላ በታካሚዉ አካል ላይ ብዙም ጉዳት እንዳይደርስ ያግዛል። ከላይ በተቀመጠዉ ምስል ላይ ይህ አይነቱ ዘዴ 5 ስብራቶችን በአንድ ቀዶ ህክምና በዶ/ር ሳሙኤ ልተከናውኖ ይታያል።

 • በቀዶ ህክምና የሚደረግ የዉስጥ ድጋፍ:

ቀዶ ህክምናን በመጠቀም ቦታቸዉን የሳቱ የአጥንት ስብብርባሪዎችን መጀመሪያ ቦታቸውን እንድይዙ ይደረጋል። ከዚያም ስብርባሪ አጥንቶችን በብረት እና ማሰሪያ ቡሉን ይያዛሉ።

በ ሃምሌ 2013 ዓ.ም በዶ/ር ሳሙኤል ኃይሉ የተዘጋጀ እና የቀረበ

*ማስታወሻ:* በዚህ ጽሁፍ የተዘጋጀዉ መረጃ ለማስተማሪያነት የሚዉል ነዉ። ይሄም ጽሁፍ ሀኪም ማማከርን ሊተካ አይገባም። በዚህ ጽሁፍ ላይ ባገኙት መረጃ ምክንያት በኃኪምዎ የታዘዙትን ምክር ወደ ጎን መተዉ አይመከርም።

Send this to a friend