የዳሌ ማቀፊያ ስብራት

ይህ ምስል የዶ/ር ሳሙኤልን ታካሚ ራጅ እና በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚያሳይ (3D) ሲቲ ስካን ሲሆን፤ ውስብስብ የሆነውን የዳሌ ራስ ማቀፊያ ስብራትን እና የስብራቶቹ በቀዶ ጥገና ወደ ቦታቸው ተመልሰው በተለያዩ ብረት እና ብሎኖችን በመጠቀም ከተሰራ በኋላ ያሳያል።

ምንድነዉ?
የዳሌ ማቀፊያ ስብራት በዳሌ መገጣጠሚያ የዳሌ ራስ መሰኪያዉ ክፍል መሰበር ነዉ። ይሄም ስብራት በትክክል ካልገጠመ እና ወደ ቦታዉ ካልተመለሰ ህመም ያለው ያለጊዜው የሚከሰት የዳሌ አንጓ ብግነትን ሊያስከትል ይችላል። በትክክል ወደ ቦታዉ ከተመለሰ በኋላም መጀመሪያ ከደረሰበት የመገጣጠሚያ ጉዳት የተነሳ ብግነቱ ሊከሰት ይችላል።

ይህ ስብራት ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ በፊት ወደ ነበረበት ለመመለስ አስቸጋሪ ነው። ስለሆነም የተሻለ ዉጤት ለማግኘት እና የዳሌ መገጣጠሚያ ቅየራ ህክምና የማስፈለግ እድሉን ለማስቀረት በህክምናዉ ከፍተኛ ልምድ ባለቸዉ ሰብ-ስፔሻሊስቶች መታከም አሌ የማይባል ልዩነት ይፈጥራል።

መንስኤ
እነዚህ ስብራቶች በሁለት የዕድሜ ክፍሎች ሊከሰት ይችላሉ፡-

 • አብዛኛዎቹ በወጣቶች ላይ የሚከሰተዉ በመኪና አደጋ ጊዜ በሚፈጠር ከፍተኛ ኃይል ባለዉ ጉዳት ሲሆን፣
 • በተወሰኑቱ እድሜያቸዉ ገፋ ባሉ ሰዎች ደግሞ ቀለል ባለ የመዉደቅ አደጋ በሳሳ አጥንት አከባቢ ላይ በሚከሰት ስብራት ነዉ።

ምልክቶች

ብዙውን ጊዜ ከስብራቱ በኋላ ህመም የሚሰማቸዉ ሲሆን ህመሙ በዳሌ መገጣጠሚያ እንቅስቃሴ ጊዜ ስለሚባባስ፤ ስብራቱ እንደተከሰተ መራመድ አዳጋች ይሆናል። ከስብራቱ ጋር የነርቭ ጉዳት በሚከሰትበት ጊዜ ደግሞ የእግር ድንዛዜ፣ የዉጋት ስሜት ወይም የእግር እንቅስቃሴ መሳን ሊከሰት ይችላል ፡፡ በከፍተኛ የኃይል አደጋ ሲከሰት ምልክቶቹም በተጎዳዉ የሰዉነት ክፍል ላይ ይታያሉ።

ምርመራ
በድንገተኛ ክፍል ከሚደረገዉ ቅድመ ህከምና እና አሰሳ በኋላ አስፈላጊዉ ምርመራ ይደረጋል።

 • ራጅ (X-ray)፡ ማንኛዉም አይነት ከፍተኛ ሃይል ያላቸዉ አደጋዎች ራጅ በመነሳት የዳሌ ማገቀፊያ አጥንት ስብራት መኖር ያለመኖሩን እንደ መጀመሪያ አሰሳ ምርመራ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
 • ሲቲ ስካን (CT Scan)፡  የራጅ ምርመራ ስብራቱን ሊያሳይ ቢችልም የሲቲ ስካን ምርመራ በተሻለ መልኩ የስብራቱን ባሄሪ ለማየት ወሳኝ ነው። የሲቲ ስካን የተወሳሰበዉን የዳሌ ማቀፊያ ስርዓተ ቅርጽ እና ስብራት ሁኔታ በጥልቀት እንድናይ ከማስቻሉም በላይ የቀዶ ህክምናዉንም በተሻለ መንገድ ለማቀድ ያግዘናል። ስብራቶቹንም በተለያዩ አቅጣጫዎች (3D) በጥልቀት እንድናይ ይረዳናል።
 • የተለያዩ የደም እና ሌሎችንም ምርመራዎችን በማድረግ ተጓዳኝ ችግር ከተከሰተ ማረጋገጥ እንችላለን።

ህክምና

የስብራቱን ህክምና ከማድረጋችን በፊት የሚከተሉትን ሁኔታዎች ማጤን ያስፈልጋል፡-

 • የስብራቱ ባህሪ
 • በስብርባሪዎቹ መካከል ያለዉ የመለያየት ርቀት ደረጃ
 • የአጥንቱ ራስ እና የዳሌ አጥንት መሰኪያ መካከል ያለዉ የግኑኝነት ለውጥ
 • የዳሌ አጥንት ራስ ከ ማቀፊያው መውለቅ
 • የታካሚዉ አጠቃላይ የጤና ሁኔታ
 • ያለ ቀዶ ህክምና የሚደረግ እርደታ
  የተወሰኑ ስብራቶች ያለ ቀዶ ህክምናዎች እርዳታ ደረግላቸዉ ይቻለሉ፡-
  • በስብራቱ ምክንያት አጥንቶቹ ቦታቸዉን ያልለቀቁ ከሆነ
  • የልብ ህመም ወይም ሌላ የጤና ችግር ባለባቸዉ ታካሚዎች ላይ በቀዶ ህክምና ምክንያት ህመማቸዉ የሚባባስ ከሆነ
  • ስብራቱ የዳሌ መገጣጠሚያን የማያናጋ ከሆነ
 • ቀዶ ህክምና እርዳታ
  • አብዛኛዎቹ የዳሌ ማቀፊያ ስብራቶች ከቀዶ ህክምናው የተሻለ ዉጤት ለማግኘት በ ሰብ-ስፔሻሊስት ቢደረግላቸዉ ይመረጣል።
  • ስብራቱ እስኪድን ድረስ አጥንቶቹን ቦታቸዉን እንዳይለቁ የሚከተሉትን ድጋፎች መጠቀም እንችላለን።
 • በትንሽ ጠባሳ የቀዶ ህክምናው ጫና መጠነኛ በሆነ መልኩ የሚደረግ
  • መጠነኛ የሆነ መናጋት ለተከሰተባውው ስብራቶች እና በዚህ መልኩ ሊስተካከሉ ለሚችሉ ስብራቶች ጥቅም ላይ ይውላል።
  • መጠናቸዉ ትንንሽ በሆኑ የቆዳ ክፍተቶች በቆዳ ስር በሚቀበሩ ብረቶች በመጠቀም ሊደረግ ይችላል። ይሄም አሰራር የደም መፍሰስን እና የቀዶ ህክምናውን ጫና በመቀነስ የማገግም ሂደቱ እነዲሳለጥ እና የቀዶ ህክምናዉን ጠባሳ አነስተኛ እንዲሆን ይረዳል።
 • በቀዶ ህክምና የሚደረግ የዉስጥ ድጋፍ
  • ቀዶ ህክምናን በመጠቀም ቦታቸዉን የሳቱ የአጥንት ስበብርባሪዎችን መጀመሪያ ቦታ እንዲይዙ ይደረጋል። ከዚያም ስብርባሪዎቹን ከአጥንቶቹ ጋር በብረት እና ማሰሪያ ብሎን ይጣበቃሉ።
  • ይህ አይነቱ ቴክኒክ ከላይ በሚታየው ራጅ ምሳሌ ተቀምጧል።
 • ሙሉ የዳሌ መገጣጠሚያ ቅየራ
  • ትኩስ ስብራቶች ወይም የዳሌ መገጣጠሚያ ብግነት ባስከተለ የዳሌ ማቀፊያ ስብራት ላይ የሙሉ ዳሌ መገጣጠሚያ ቅየራ እንደ መጨረሻ የህክምና አማራጭ ሊወሰድ ይችላል።
  • የዳሌ ማቀፊያ ጉዳት ከባድ ሲሆን እና የማስተካከሉ ቀዶ ህክምና ከጊዜ ብዛት ዉጤታማነቱ አጠያያቂ ከሆነ ሙሉ ዳሌ ቅየራ በአዲስ ስብራት ላይ ተመራጭ ሊሆን ይችላል።
  • ስብራቶቹ በቆዶ ህክምና ከተስተካከሉ በኋላ በሚከሰት አንጓ ብግነት ጊዜ ሙሉ ዳሌ ቅየራ እንደተሻለ አማራጭ ይወሰዳል።

በ ሃምሌ 2013 ዓ.ም በዶ.ር ሳሙኤል ኃይሉ የተዘጋጀ እና የቀረበ

*ማስታወሻ:* በዚህ ጽሁፍ የተዘጋጀዉ መረጃ ለማስተማሪያነት የሚዉል ነዉ። ይሄም ጽሁፍ ሀኪም ማማከርን ሊተካ አይገባም። በዚህ ጽሁፍ ላይ ባገኙት መረጃ ምክንያት በኃኪምዎ የታዘዙትን ምክር ወደ ጎን መተዉ አይመከርም።

Send this to a friend