የዳሌ አጥንት ስብራት

የዳሌ አጥንት ስብራት

ምንድነዉ?
የዳሌ አጥንት ስብራት ማለት የታፋ አጥንት ላይኛዉ ክፍል ላይ የሚከሰት ስብራት ነዉ። ስብራቱም የታፋ አጥንት ራስን እና ከሱ ስር ያሉትን ክፍሎች ያካትታል፡-
• የታፋ አጥንት አንገት(ላይኛዉ ክፍል)
• ኢንተርትሮካንተሪክ (በሁለቱ የታፋ አጥንት ራስ ላይ የሚገኙ አጥንት ጉብታዎች መካከል)
• ሰብትሮካንተሪክ (የታፋ አጥንት ራስ ላይ ካሉ ጉብታዎች በስር በኩል )
የታፋ አጥንት አንገት (ላይኛዉ ክፍል) ስብራት ከ ዳሌ አጥንት ስብራቶች በብዛት የሚከሰተዉ ነዉ።
መንስኤ
አብዛኛዎቹ የአጥንት ስብራት መንስኤ እድሜያቸዉ ገፋ ባሉ ሰዎች ላይ አጥንት ከመሳሳት የተነሳ የሚከሰት ነዉ። በወጣቶች ላይ የሚከሰተዉ የዳሌ ስብራት ደግሞ ከፍተኛ በሆነ ኃይል ተከትሎ በመኪና አደጋ ወይም ከከፍታ በመዉደቅ ነዉ።

ምልክቶች
• በአብዛኛዉ የሚታየዉ ምልክት በንፍፍት አከባቢ እና ላይኛዉ ታፋ ላይ የሚሰማ ህመም
• የላይኛዉን የእግር ክፍል ወይም ጉልበት ማንቀሳቀስ ያለመቻል
• የእግር ወደ ዉጭ መዞር
• በተሰበረዉ ዳሌ ጎን መቆም ወይም መራመድ ያለመቻል ናቸዉ

ምርመራ
የዳሌ ገንዳ ራጅ አብዛኞቹን የዳሌ ስብራቶች የሚያሳይ ቢሆንም እንደየአስፈላጊነቱ ሲቲ ስካን ወይም ኤም አር አይ ሊታዘዝ ይችላል።

ህክምና
አብዛኛዎቹ የዳሌ ስብራቶች ቀዶ ህክምና በ አንድ ወይም ሁለት ቀናት ቁስጥ ያስፈልጋቸዋል። ባለባቸዉ ህመም ምክንያት ቀዶ ህክምና ማድረግ ከማይችሉት ታካሚዎች መካካል ጥቂቶቹ ያለ ቀዶ ህክምና ሊታከሙ ይችላሉ።
የቀዶ ህክምናዉም አላማ ታከሚዎቹ በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ እና ረዘም ላለ ጊዜ አልጋ ቁራኛ በመሆን ከሚከሰቱ ችግሮች ማለትም፤ የተኙበት የሰዉነት ክፍል ቁስለት፣ የደም መርጋት፣ የሳምባ ምች፣ ድንገተኛ የልብ መቆም እና ህልፈተ ህይወትን ለመታደግ ይደረጋል።
የቀዶ ህክምናዉም ጊዜ ታካሚዎቹ ያለባቸዉ የጤና ችግሮች ቀዶ ህክምናን ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ እስከፈጠር በመታገስ ይሆናል። ቀዶ ህክምናዉን በአጭር ጊዜ ማድረጉ የሚከተሉትን ችግሮች ለመቀነስ ይረዳል። ቀዶ ህክምናዉን በ 48 ሰዓት ዉስጥ ለማከናወን አስፈላጊዉን ሁሉ ስለምናደርግ የጤና ሁኔታን ባማከለ ወደ ቀዶ ህክምና መግባቱ ይመከራል።

ቀዶ ህክምናዉ የሚወሰንባቸዉ ሁኔታዎች፡-
• የስብራቱ አይነት
• የስብራቱ ቦታ
• የታካሚዉ ዕድሜ
• የታካሚዉ እንቅስቃሴ ሁኔታ
• አጠቃላይ የታካሚዉ ጤንነት ደረጃ ናቸዉ።

የታፋ አጥንት አንገት ስብራት
ይሄኛዉ ስብራት ከሁሉም የዳሌ አጥንት ስብራቶች በብዛት የሚከሰት ነዉ። አብዛኛዎቹ ስብራቶች በቀዶ ህክምና የሚታከሙ ሲሆን፣ ከስብራቱ በፊት መራመድ የማይችሉ እና ከባድ የጤና ችግር ያለባቸዉ ታካሚዎች ያለ ቀዶ ህክምና ሊረዱ ይችላሉ።

በወጣት ታካሚዎች በተቻለ መጠን የተፈጥሮዉን የላይኛዉ ታፋ አጥንት ራስ ማቆየት ይመከራል። የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ስብራቶችን ቀዶ ህክምና እናደርጋለን። ከነዚህም መንገዶች መካከል በቀዶ ህክምና ወይም ያለ ቀዶ ህክምና የተሰባሩ አጥንቶችን በቦታቸዉ በመመለስ በተለያዩ ብረቶች ማሰር ያካትታል። እነዚህ መንገዶች ለሊያስከትሉ የሚችሉት ችግሮች ቢኖሩም በተቻለ መጠን በወጣት ታካሚዎች የተፈጥሮዉን የዳሌ አጥንት ማቆየት ይመከራል። ከቀዶ ህክምና በኋላ አጥንቱ የማይድን ከሆነ እና ችግሮች የሚከሰቱ ከሆነ የዳሌ ቅየራ አማራጭ ይሆናል።

እድሜያቸዉ ገፋ ባሉ ታካሚዎች ህክምናዉ ከግማሽ እስከ ሙሉ ዳሌ ቅየራ ድረስ ሊሆን ይችላል።
ዶ.ር ሳሙኤልም ጉዳቱ መጠነኛ የሆነ ቀዶ ህክምናን ወይም ዳሌ ቅየራን እንደ አስፈላጊነቱ ከታካሚዉ ሁኔታ እና ፍላጎት በመነሳት አማራጮችን በመመካከር ቀዶ ህክምናዎችን ያደርጋሉ። ጉዳቱ መጠነኛ የሆነ ቀዶ ህክምና የስብራቶቹን ህክምና የተሻለ ስላደረገዉ የመገገሚያ ጊዜን፣ የሆፒታል ቆይታን እና የሚከተሉት ጉዳቶች ላይ ከፍተኛ መሻሻልን አምጥቷል።

ስለ ስብራቱ ቀዶ ህክምና የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖርዎ ከስር በዶ.ር ሳሙኤል የተዘጋጀዉን ቪድዮ ይመልከቱ።

በላይኛዉ የታፋ አጥንት ላይ በሚገኙ ገብታዎቸ መካከል የሚከሰት ስብራት (Intertrochanteric fracture)
ይሄኛዉ ስብራት በስሙ እንደተጠቀሰዉ በላይኛዉ የታፋ አጥንት አንገት ስር ባሉ ትልቁ እና ትንሹ ተብለዉ በሚታወቁ ጉብታው መካከል የሚከሰት ስብራት ነዉ። እነዚህንም ጉብታዎች በዳሌ አጥንታችን ጎን በኩል በመዳሰስ ማስተዋል ይቻላል።

ይሄኛዉ ስብራት የሚታከመዉ በቀዶ ህክምና ስሆን በዳይናሚክ የዳሌ ቡሉን፣ ወይም አንግል ብሌድ ማሰሪያ ወይም በአጥንቱ ዉስጥ በሚገባ ብረት ይሆናል። ዳይናሚክ የዳሌ ቡሎን እና አንግል ብሌድ ማሰሪያ በዉጨኛዉ የላይኛዉ የታፋ አጥንት ላይ የሚታሰሩ ሲሆን ብረቱ አካል ደግሞ በላይኛዉ የታፋ አጥንት ራስ እና አንገት ዉስጥ ይገባል።

በአጥንቱ ዉስጥ የሚገባዉም ብረት በአጥንቱ መቅኔ ቀዳዳ ዉስጥ በላይኛዉ የአጥነቱ ጉብታ በኩል በሚበሳዉ ቀዳዳ እንዲገባ ይደረጋል። ከዚያም አንድ ወይም ከዚያ በላይ ቡሎን ማሰሪያዎች በብረቱ ዉስጥ በ አጥንቱ ራስ እና በላይኛዉ የታፋ አጥንት የስረኛዉ ክፍል በማስገባት ይታሰራሉ።

ከጉብታዎቹ ስር የሚከሰት ስብራት (Subtrochanteric Fracture)
ከገብታዎቹ ስር የሚከሰተዉ ስብራት ከዳሌ መገጣጠሚያ በታች የሚገኘዉን የላይኛዉን የታፋ አጥንት ክፍል ስብራት የሚያካትት ነዉ። ይሄኛዉ ስብራት የሚታከመዉ እንደየ ስብራቱ ሁኔታ፣ የአጥንቱ ሁኔታ እና እንቅስቃሴ መጠን ላይ በመመስረት፤ በዳይናሚክ የዳሌ ቡሉን፣ ወይም አንግል ብሌድ ማሰሪያ ወይም በአጥንቱ ዉስጥ በሚገባ ብረት ይሆናል።

የላይኛዉ የታፋ አጥንት ራስ ስብራት (Femur Head Fractures)
የላይኛዉ የታፋ አጥንት ራስ ስብራት አብዛኛዉን ጊዜ ከፍተኛ ፍጥነት እና ኃይል በሚያስከትሉ አደጋዎች መንስኤነት ይከሰታል። ይሄም ስብራት ከ ዳሌ አጥንት ዉልቃት ወይም ከዳሌ አጥንት ሶኬት ስብራት ጋር ሊከሰት ይችላል።

የህክምና አማራጮች፡

• ቦታዉን ያልሳተ እና ክብደት በማይሸከም የአጥንቱ ክፍል ላይ ከሆነ ያለ ቀዶ ህክምና ሊታከም ይችላል።
• ስብርባሪዎቹ የዳሌ መገጣጠሚያ ላይ የሚደቀኑ ወይም ሰፋ ያለ ቦታ ያልያዙ ከሆነ ማስወገድ ሊያስፈልግ ይችላል።
• በወጣት እና ብዙ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ታካሚ ላይ የሚከሰቱ ትልልቅ ስብርባሪዎች በቀዶ ህክምና ቦታቸዉን ሊይዙ ይገባል።
• እድሜያቸዉ ገፋ ባሉ ታካሚዎች የሚከሰቱ ትልልቅ ስብርባሪዎቸ ግን ግማሽ ወይም ሙሉ የዳሌ ቅየራ ሊያስፈልጋቸዉ ይችላል።

በ ሃምሌ 2013 ዓ.ም በዶ.ር ሳሙኤል ኃይሉ የተዘጋጀ እና የቀረበ

*ማስታወሻ:* በዚህ ጽሁፍ የተዘጋጀዉ መረጃ ለማስተማሪያነት የሚዉል ነዉ። ይሄም ጽሁፍ ሀኪም ማማከርን ሊተካ አይገባም። በዚህ ጽሁፍ ላይ ባገኙት መረጃ ምክንያት በኃኪምዎ የታዘዙትን ምክር ወደ ጎን መተዉ አይመከርም።