የዳሌ ገንዳ ስብራት

የዳሌ ገንዳ ከላይኛው የሰውነት ክፍል የለያየ ስብራት ሲቲ ስካን እን ስብራቱ በትንሽ ጠባሳ በዶ/ር ሳሙኤል ኃይሉ ከተሰራ በኋላ።

ምንድነዉ?

የዳሌ ገንዳ ወገብን ከእግሮች ጋር የሚያገናኝ ክብ (ቀለበት) ሰርተው የተቀመጡ የአጥንቶች ክፍል ነዉ። የዳሌ ገንዳ ስብራት ተብሎ የሚጠራዉ ክብ መሰል የዳሌ ገንዳን አጥንት ከሚሰሩት ክፍሎች የአንዳቸዉ መሰበር ነዉ። ከፍተኛ ሃይል ያለዉ አደጋ አንደኛዉን የአጥንቱን ክፍል በሚሰብርበት ጊዜ በአብዛኛዉ በተቃራኒዉ የክቡ ክፍል ስብራት ሊከሰት ይችላል።

መንስኤዉ

የዳሌ ገንዳ ስብራት ከሚያስከስቱ ምክንያቶች መካከል፡-

 • በእድሜ ገፋ ያሉ እና የአጥንት መሳሳት ችግር ያለባቸዉ ሰዎች ላይ ቀለል ያለ የመዉደቅ አደጋ ተከትሎ፥ ወይም
 • እንደ መኪና አደጋ እና ከከፍታ ላይ መዉደቅን የመሰሉ ከፍተኛ ሃይል ያላቸዉ አደጋዎች የዳሌ ገንዳ ስብራት ሊከሰት ይችላል።


ምልክቶች
የዳሌ ገንዳ ስብራት ምልክቶች እንደየስብራቱ መጠን ቢለያዩም፣ በአብዛኛዉ ስብራቶችን ተከትሎ የህመም ስሜት ይከሰታል።

 • በዉስጠኛዉ የታፋ ክፍል፣ ዳሌ አካባቢ፣ ወገብ ወይም መቀመጫ አካባቢ ሳይነካም ሆነ ሲነካ የሚሰማ የህመም ስሜት
 • የዳሌ ገንዳ አጥንት አከባቢ መበለዝ ወይም እብጠት
 • በመቀመጥ ጊዜ ወይም አይነምድር በማስወገድ ጊዜ የሚከሰት ህመም
 • በመዋለጃ ክፍሎች ወይም የታችኛዉ የሰዉነት ክፍሎች መደንዘዝ ወይም ስሜት ያለመሰማት
 • የስብራቱ ደረጃ እጅግ ከባድ ሲሆን መራመድ ወይም መንቀሳቀስ የማይታሰብ ይሆናል
 • ከሰዉነት ዉጭ የሚፈስ ወይም ወደ ዉስጥ በመፍሰስ ታካሚዉ ራሱን የሚስት ደም መፍሰስ ሊያስከትል ይችላል።

ምርመራ

 • ራጅ (X-ray)፡ ማንኛዉም አይነት ከፍተኛ ሃይል ያላቸዉ አደጋዎች ራጅ በመነሳት የዳሌ ገንዳ ስብራት መኖር ያለመኖሩን እንደ መጀመሪያ ምርመራ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
 • ሲቲ ስካን (CT Scan)፡ የተለያዩ የአጥንት ስብራቶች መኖራቸዉን የራጅ ምርመራ ሊያሳይ ቢችልም የሲቲ ስካን ምርመራ በተሻለ መልኩ የስብራቱን ባሄሪ ለማየት አንዱ አማራጭ ነው። የዳሌ ገንዳ አጥንት ለእይታ ዉስብስብ አጥንት በመሆኑ ስብራቶችን በጥልቀት ማስተዋል እንድንችል እና ከስብራቱ ጋር የተያያዙ የዉስጥ የሰዉነት ክፍሎች ጉዳት መኖራቸዉን ሊያሳይ ይችላል። ስብራቶቹንም በተለያዩ አቅጣጫዎች (3D) በጥልቀት እንድናይ ጭምር ሊረዳን ይችላል።
 • አልትራሳዉንድ(Ultrasound):ሲቲ ስካን ምርመራ በፍጥነት ማግኘት በማይቻልበት ሁኔታ ወይም እንደየ ጉዳቱ ሁኔታ አልተራሳውን ሊያስፈልግ ይችላል።
 • ኤም አር አይ (MRI)፡ እንደየ አስፈላጊነቱ የ ኤም አር አይ (MRI) ምርመራዎችን ልንጠቀም እንችላለን።
 • ዴክሳ ሰካን (dual-energy X-ray absorptiometry (DXA)፡ አጥንት መሳሳት ጋር ተያይዞ የሚከሰት የዳሌ ገን ዳስብራት በሚኖርበት ጊዜ የ ዴክሳ ስካን ምርመራ በመጠቀም የአጥንቶቹን የመሳሳት ደረጃ ይዘት ማየት እንችላለን።
 • የተለያዩ የደም ምርመራዎችን በማድረግ የፈሰሰዉን የደም መጠን ማወቅ፣ የጉበት ወይም ኩላሊት ጉዳት መኖሩን እናም የሽንት ምረመራን በማድረግ ደግሞ የሽኝት ቧንቧ ጉዳት መኖር ያለመኖሩን ማረጋገጥ እንችላለን።

ህክምና
የዳሌ ገንዳ ስብራት በሚከሰትበት ጊዜ የህክምናዉን አይነት ከሚወስኑ ምክንያቶች መካከል፡-

 • የዳሌ ገንዳ አጥንት ቀለበት አጥንቶች ቦታቸዉን መልቀቃቸው
 • የደም መፍሰስ መቆም ያለመቆም እና የታካሚዉ ጤንነት ደረጃ
 • የስብራቱ ቦታ እና
 • ከስብራቱ ጋር የተያያዙ የዉስጥ ሰዉነት ክፍል አደጋዎች መኖር ያለመኖራቸዉ ይገኙበታል።
 • ህይወትን የመታደግ ህክምናዎች
  የዳሌ ገንዳ ስብራት ለማቆም የሚከብድ የደም መፍሰስ ሲኖር እና የአጥንቶቹ ቦታ መሳት የሚያስከትል ከሆነ ህይወትን አደጋ ዉስጥ ሊያስገባ የሚችል ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል። በዚህም ጊዜ በፍጥነት ወደ ህክምና ቦታ መድረሱ ወሳኝ ነዉ። ይህ ሁኔታ በሚከሰትም ጊዜ የህክምናዉ አላማ የታካሚዉን ህይወት መታደግ ይሆናል። ዋነኛዉ ትኩረታችንም የተለያዩ አጥንስብራት ውም ውልቃቶችን ወደ ቦታቸዉ እንዲመለሱ ማድረግ፣ የደም መፍሰሱን ማቆም እና የፈሰሰዉን ደም መተካት ይሆናል።
  • ህይወትን አደጋ ዉስጥ ሊከት የሚችለዉን ሁኔታ ካስወገድን በኋላ አጥነቶቹን በተቻለ መጠን ትክክለኛ ቦታ በማስያስዝ ስብራቱ መዳን እንዲችል ማድረግ ላይ እናተኩራለን።
 • ያለ ቀዶ ህክምና የሚደረግ እርዳታ
  የአጥንቶች ቦታ መሳት የማይታይበት የዳሌ ገንዳ ስብራት ያለቀዶ ህክምና እርዳታ ሊደረግበት ይችላል።
 • የቀዶ ህክምና እርዳታ
  ዶክተር ሳሙኤል ህይወትን አደጋ ዉስጥ በሚከቱ እና ዉስብስብ የዳሌ ገንዳ ስብራቶች ህክምና በሃገራችን የዳበረ ልምድ አካብተዋል። በህክምናዉም ዘርፍ በኢትዮጵያ በሰብ-ስፔሻሊስት ደረጃ የተማሩ የመጀመሪያዉ ባለሙያ እንደመሆናቸዉ መጠን በዉጭ ሀገር የቀሰሙትን ልምድ በሀገራችንም እንዲስፋፋ አድርገዉታል። ለዚህም አስተዋጿቸዉ ከኢትዮጵያ አጥንት ህክምና እና አደጋዎች ሃኪሞች ማህበር ሽልማት በ መጋቢት 2017 እ.ኤ.አ ተበርክቶላቸዋል። ይሄንንም የህክምና ልምድ ለኢትዮጵያዉያን እና አፍሪካዉያን አጥንት ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሃኪሞች በማስተማር ላይም ይገኛሉ። በዘርፉም በአለም አቀፍ ደረጃ የአጥንት ሃኪሞች ማህበረተሰብ ልምዳቸዉን ያካፍላሉ።

ከስር በሚገኘዉ ቪድዮ የመዋዕለ ንዋይ ችግር በሚታይበት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቀዶ ህክምናዉን እንዴት እንደሚያከናዉኑ ይመልከቱ።

በ ሃምሌ 2013 ዓ.ም በዶ.ር ሳሙኤል ኃይሉ የተዘጋጀ እና የቀረበ

*ማስታወሻ:* በዚህ ጽሁፍ የተዘጋጀዉ መረጃ ለማስተማሪያነት የሚዉል ነዉ። ይሄም ጽሁፍ ሀኪም ማማከርን ሊተካ አይገባም። በዚህ ጽሁፍ ላይ ባገኙት መረጃ ምክንያት በኃኪምዎ የታዘዙትን ምክር ወደ ጎን መተዉ አይመከርም።

Send this to a friend