ሙሉ የጉልበት ቅየራ

ራጆቹ 17 ዓመት የቆየ መጨረሻ ደረጃ የደረሰ የጉልበት ችግርን፤ እና ዶ/ር ሳሙኤል የሰራውን የሙሉ የጉልበት መገጣጠሚያ ቅየራ ያሳያል።

ጉልበትዎ በመገጣጠሚያ ብግነት ምክንያት እጅግ ከተጎዳ ቀለል ያሉ የዕለተለት እንቅስቃሴዎችን ማለትም መራመድ እና ደረጃ መዉጣት ከባድ ሊሆንብዎ ይችላል። ከዚያም ቀስ በቀስ ሳይንቀሳቀሱ ተቀምጠዉም ሆነ ተጋድመዉ ህመም ሊሰማዎት ይችላል።

ከቀዶ ህክምና ዉጪ ያሉ መፍትሄዎች ማለትም መድሃኒቶች፣ በጉልበት የሚሰጡ መርፌዎች እና የመራመጃ ድጋፎች እምብዛም ወደ ማይጠቅሙበት ደረጃ ከደረሱ የጉልበት ቅየራ ህከምናን እንደመፍትሄ ሊወስዱ ይችላሉ። የጉልበት መገጣጠሚያ ቅየራ ቀዶ ህክምና የህመም ስቃይን ለመቀነስ፣ የተወላገደ እግርን ለማስተካከል፣ በበቂ ሁኔታ እንቅስቃሴ ለማድረግ እና ወደ ዕለተለት ስራ ለመመለስ ዉጤታማ እና ተመራጭ መፍትሄ ነዉ።

በአብዛኛው ለረጅም ጊዜ የሚጠኑ የጉልበት ህመሞች እና የጉልበት እንቅስቃሴ መገደብ መንስኤ ቁርጥማት ነዉ። አብዛኞቹ የጉልበት ህመሞች በአጥንት መገጣጠሚያ ብግነት፣ የሪውማቶይድ ቁርጥማት እና ከአደጋ ወይም ምት በኋላ የሚከሰቱ ቁርጥማቶች ናቸዉ።

የጉልበት ቅየራ የጉልበትን መገጣጠሚያ የሚሰሩ አጥንቶች የጫፍ ክፍል ብቻ መተካት ስለሆነ በተሻለ ሁኔታ የጉልበት ሽፋን ቅየራ (Resurfacing) በሚለዉ ሊገለጽ ይችላል።

የጉልበት ቅየራ ቀዶ ህክምናዉም የሚከናወነዉ የተጎዳዉን የታፋ አጥንት(Femur) እና የእግር አጥንት(Tibia) ጫፍ መሸፈኛ ካርቲሌጅ ከስራቸዉ ካለዉ ጥቂት አጥንት ጋር በማስወገድ ሰዉ ሰራሽ በሆነ ብረት በመተካት ነዉ። በሁለቱ አጥንቶች መካከል በቂ የሆነ እንቅስቃሴ እንዲኖር እና አላስፈላጊ ፍትጊያ በተቀየሩት ብረቶች መካከል እንዳይከሰት በተራቀቀ የህክምና ደረጃ በተዘጋጀ ፕላስቲክ በላይኛው እና ታችኛው የጉልበት ክፍል መካከል ይገባል። የጉልበት ሎሚ (Patella) የስረኛዉ ክፍል እንደ አስፈላጊነቱ ቅርፁን በማስተካከል ከተቀየረው ጉልበት ቅርፅ እንዲመሳሰል ማስተካከያ ሊደረግበት (patelloplasty) ወይም የታችኛው ክፍል በትላስቲክ እንዲለብስ ይደገጋል (resurfacing)።

ከቀዶ ህክምናዉ በኋላ ስለምንጠብቀው ለዉጥ ተገቢ መረጃ እንዲኖረን ያስፈልጋል። አብዛኞቹ ጉልበት ቅየራ የተደረገላቸዉ ታካሚዎች ከህመማቸዉ መሻልን እና የዕለተለት እንቅስቃሴዎቻቸዉን ላይ መሻል ያሳያሉ።

በቀንተቀን እንቅስቃሴ እና አጠቃቀም፣ የስውሰራሹ ጉልበት ፕላስቲክ ክፍል በጊዜ ብዛት እየተበላ መሄዱ አይቀርም። ስለዚህ ከመጠን በላይ የሆኑ ክብደት መሸከም፣ ዝላይ፣ ሩጫ ወይም ሌሎች መሬትን በክፍተኛ ሃይል በዕግር መግጨትን የሚያስከትሉ እንቅስቃሴዎች እና ስፖርቶች የተቀየረዉን ጉልበት እድሜ ሊያሳጥሩ ስለሚችሉ በተቻለ መጠን ከህክምናዉ በኋላ አይመከሩም።

ዶ/ር ሳሙኤል በሀገረ አሜሪካ በተመረቱ የሰዉ ሰራሽ የጉልበት መቀየሪያዎችን በመጠቀም የጉልበት ቅየራ ቀዶ ህክምናዉን ያከናዉናል። አብዛኞቹ ታካሚዎቻችንም በቀዶ ህክምናዉ እለት ወደ ሆስፒታል በመግባት ከቀዶ ህክምናዉ በኋላ በ ሁለት ቀን ከሆስፒታል ይወጣሉ። ከሰራቸው መገጣጠሚያ ቅየራዎች መካከል የአንዱን ታካሚ ለውጥ በዚህ ቪዲዮ መመልከት ይችላሉ።

እያንዳንዱ ታካሚ የራሱ የሆነ የማገገም ሂደት እና ጊዜ ቢኖረዉም አብዛኞቹ ታካሚዎቻችን ግን ከ 2 እስከ 3 ወር ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ከቀዶ ህክምና በፊት ወደ ነበረዉ እለትተዕለት ስራቸዉ ይመለሳሉ። 

የጉልበት ቅየራ ህክምና እንዲደረግልዎ ካሰቡ ወይም በሃኪም ከተመከሩ ከ ዶ/ር ሳሙኤል ጋር ስለ አስፈላጊነቱ እና የክንውን ሂደቱ በጥልቅ መምከር ያስፈልግዎታል።

እያንዳንዱ ቀዶ ህክምና የራሱ የሆነ የጎንዮሽ ጠንቅ ሊኖረው ስለሚችል የቀዶ ህክምናዉን ተጓዳኝ ችግሮች ስጋት መቀበል ከሀኪምዎ ጋር በተገቢው መልኩ መምከሩ የተመከረ ነዉ።

በ ሃምሌ 2013 ዓ.ም በዶ.ር ሳሙኤል ኃይሉ የተዘጋጀ እና የቀረበ

*ማስታወሻ:* በዚህ ጽሁፍ የተዘጋጀዉ መረጃ ለማስተማሪያነት የሚዉል ነዉ። ይሄም ጽሁፍ ሀኪም ማማከርን ሊተካ አይገባም። በዚህ ጽሁፍ ላይ ባገኙት መረጃ ምክንያት በኃኪምዎ የታዘዙትን ምክር ወደ ጎን መተዉ አይመከርም።

Send this to a friend