የዳሌ ራስ መበስበስ

የ MRI ምስሎቹ የዳሌ ራስ ቅርፅ ሳይቀየር (ከላይ በኩል) እና የዳሌ ራስ ቅርፅን ያስቀየረ የዳሌ ራስ መበስበስ (ከታች በኩል) ያሳያሉ።.
በስተቀኝ በኩል የላይኛው ራጅ የተፈጥሮ የዳሌ ራስን የደም ዝውውር እንዲመለስ የሚደደረግ ቀዶ ህክምናን ያሳያል፤
ታችኛው የባሰ ደረጃ የደረሱ የሁለቱም ሙሉ ዳሌ መገጣጠሚያ በአንዴ በዶ/ር ሳሚ ከተሰራ በኋ ላ የሚያሳይ ራጅ ነው።

ምንድነዉ?
አጥንት ህይወት ያለዉ የሰዉነታችን ክፍል ሲሆን በህይወት ለመቆየት ጤነኛ የደም ዝውውር ያስፈልገዋል። ለዚህም ወደ ዳሌ አጥንት አናት (ራስ) የሚሄዱት የደም ስሮች በዳሌ አጥንት አንገት አከባቢ ይገኛሉ። ይህም ቦታ ስብራት ወይም አደጋ በሚደርስበት ጊዜ አጠገቡ ላይ ያሉ የደም ስሮች በመጉዳት ወደ ዳሌ ራስ የሚደረሰዉን የደም ዝውውር በመዝጋት መሞት ይጀምራል። ይህም የዳሌ ራስ መበስበስ ተብሎ ይጠራል።

መንስኤ
ማንኛዉም ወደ ዳሌ አጥንት ደም እንዳይደርስ የሚያደርግ አደጋ በሙሉ የዳሌ ራስ መበስበስን ሊያስከትል ይችላል።

በሀገራችን በብዛት ከሚታዩ ምክንያቶች መካከል ፡-
• የዳሌ ራስ የደም ዝውውር ላይ በቀጥታ ጉዳት ሲደርስበት። የዳሌ አካባቢ ስብራት ወይም ኳስ የሚመስለዉ የዳሌ ራስ ከማቀፊያው በሚወልቅበት ጊዜ የደም ዝውውር ሊስተጓጐል ይችላል። ከአደጋ በኋላም የዳሌ ራስ መበስበስ እስኪከሰት ድረስ ረዘም ያሉ ወራቶች ሊያልፉ ይችላሉ።
•አንዳንድ ህክምናዎችን ተከትሎ ሊከሰትም ይችላል፤ ለምሳሌ፡- ስቴሮይድ፣ የካንሰር መድሃኒቶች፣ የጨረር ህክምና እና የእካል ንቅለ ተከላ ይገኙበታል።
• ሲጋራ ማጨስ
• የአልኮል መጠጥ ሱስ
• ኤች. አይ. ቪ.
• ሪህ
• የደም ካንሰር ይገኙበታል።

ምልክቶቹ
ቀዳሚዉ የዳሌ አጥንት ራስ መበስበስ ምልክት ህመም ነዉ። ህመሙም ብሽሽት አከባቢ፣ መቀመጫ ላይ ብሎም በታፋችን በፊትለፊት በኩል እና ጉልበት ላይ ሊሰማ ይችላል። ህመሙም በመራመድ ጊዜ ሊጨምር የሚችል ሲሆን በኋላም ወደ ማነከስ፣ የእግር እጥረት፣ የዳሌ መገጣጠሚያ እንቅስቃሴ መገደብ እና ሳይነቀሳቀሱ ረፍት ሆነ እንቅልፍ ሊነሳ ይችላል። ብሎም የለት ተለት እንቅስቃሴን አዳጋች በማድረግ የአልጋ ቁራኛ ሊያደርግ ይችላል። ብዙ ጊዜ በሁለቱም የዳሌ አጥንቶች የሚከሰት ቢሆንም ነገር ግን አደጋን ተከትሎ በሚመጣዉ የዳሌ ራስ መበስበስ አደጋዉ የደረሰበት ዳሌ ብቻ ላይ ሊከሰት ይችላል።

ምርመራ
ችግሩን ለማወቅ የሚታዩትን ምልክቶች በደምብ በማጤን፤ ሊያጋልጡ የሚችሉ ምክንያቶችንም በመፈተሽ፤ አካላዊ ምርመራ በማድረግ እና ራጅ በመነሳት ነዉ። በመጀመሪያዎቹ ሁለት የህመሙ ደረጃዎች በራጅ ላይታይ ስለሚችል ኤም አር አይ (MRI) ምርመራ እንጠቀማለን። ይህም ችግሩ ወደከፋ ደረጃ ሳይደርስ የዳሌ አጥንቱን መታደግ እንድንችል ያግዘናል።

ህክምናዉ

ህክምናዉም ችግሩ ምንያህል እንደቆየ እና ታካሚዉ ላይ ባለዉ የምልክት ደረጃ ይወሰናል።

የህክምናዉን መንገድ ከመምረጣችን በፊት ልናጤናቸዉ ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል:
• የታካሚዉ እድሜ
• የእንቅስቃሴ ደረጃ
• አጠቃላይ አካላዊ ጤና
• የእድሜ ጣሪያ ግምት
• መንስኤዉ ወይም የተገኘዉ አጋላጭ ሁኔታ እና
• የህመሙ ደረጃ ይገኙበታል።

ያለ ቀዶ ህክምና
የህመም ማስታገሻ መድሀኒቶችን መጠቀም ህመሙን ለመቀነስ ይረዳል።
ቢስፎስፎኔትየተሰኘዉ ለአጥንት መሳሳት የሚታዘዘዉ መድሃኒት ወይም የደም ማቅጠኛ መድሃኒቶች የአጥንቱን ራስ መበስበስ እድል በተወሰነ መልኩ ሊቀንሱት ይችላል።

ቀዶ ህክምና

የተፈጥሮ ዳሌን ለማትረፍ የሚደረግ

የበሰበሰውን የ ዳሌ ራስ የመብሳት ሂደት የሚያሳይ ምስል።

የዳሌ ራስ መበስበስ ባልባሰ ደረጃ ሲታወቅ (ደረጃ 1 እና 2 ላይ እያለ)፥ የደም ዝውውሩን ሊመልስ እና የሞቱትን ህዎሳቶች ሊተካ የሚችል ቀዶ ህክምና ይደረጋል። ይህም በዳሌ ጎን በኩል በሚደረግ በትንሽ ጠባሳ ይከናወናል።

የበሰበሰውን የ ዳሌ ራስ አጥንት በመብሳት ይከናወናል። ይህም ኮር ዲኮምፕረሽን (core decompression) ይባላል።

ከዛም ከታካሚው ጤነኛ የአጥንት ክፍል ህይወት ያላቸውን ህዋሳት በመውሰድ የበሰበሰው ቦታላይ እንጨምራለን።

የበሰበሰውን አጥንት መብሳት

(1) አዲስ የደም ስር የሞተው ቦታላይ እንዲያድግ ይረዳል፤ በተጨማሪም

(2) የበሰበሰው የዳሌ ራስ ክፍል ላይ ያለውን የታመቀ ግፊት እንዲተነፍስ ለማድረግ ይጠቅማል። ይህም በግፊት ጫና ብዛት ምክንያት ታካሚው ላይ ይከሰት የነበረውን ህምም ለመቀነስ ያገለግላል።

ዶ/ር ሳሚ ይህን አይነት ህክም ና የሆስፒታል አልጋ መያዝ ሳያስፈልክ በተመላላሽ ህክምና ላይ ላሉ ታካሚዎች ያከናውናል። ቀዶ ህክምናውም በተሰራበት ቀን ወደቤት መመለስ የሚችሉ ሲሆን ለ6 ሳምንታት (ወር ተኩል) ለሚያክል ጊዜ በአካል ድጋፍ እንዲንቀሳቀሱ እናደርጋለን።

አርቴፍሻል የዳሌ መገጣጠሚያ ቅየራ
የዳሌ አጥንት ራስ መበስበሱ ደረጃ 3 እና ከዚያ በላይ ከሆነ በላይ ከሆነ፥ የተፈጥሮ መገጣጠሚያውን ለማትረፍ የሚረዳ አመርቂ የሆነ ቀዶ ህክምና ስለሌለ ሙሉ ዳሌ መገጣጠሚያ ቅየራ እንደ ዘላቂ መፍትሄ ይወሰዳል።

ዶ/ር ሳሙኤልም የጉዳት ደረጃዉ ዝቅ ባለ በፊትለፊት በኩል ጡንቻ ሳይቆረጥ በሚደረግ ቀዶ ህክምና ሙሉ ዳሌ ቅየራን ያከናዉናል። ይሄም የማገገም ሂደቱን እና ህክምናዉን የተሻለ አድርጎታል። የዳሌ ራስ መበስበስ በሁለቱም እግሮች ላይ በአብዛኛው ስለሚከሰት ሁለቱንም የዳሌ ቅየራ እድደአስፈላጊነቱ በአንድ ጊዜ ማድረግ ያስችላል።

ከስር ባለዉ ቪድዮ ዶ/ር ሳሙኤል በፊት ለፊት በኩል በሚደረግ የቀዶ ህክምና ሁለቱም የዳሌ ራስ መብስበስ ህመም ያለበትን ወጣት ሲያክመዉ ይመልከቱ።

በ ሃምሌ 2013 ዓ.ም በዶ.ር ሳሙኤል ኃይሉ የተዘጋጀ እና የቀረበ

*ማስታወሻ:* በዚህ ጽሁፍ የተዘጋጀዉ መረጃ ለማስተማሪያነት የሚዉል ነዉ። ይሄም ጽሁፍ ሀኪም ማማከርን ሊተካ አይገባም። በዚህ ጽሁፍ ላይ ባገኙት መረጃ ምክንያት በኃኪምዎ የታዘዙትን ምክር ወደ ጎን መተዉ አይመከርም።